መጠጥና ስካር

ሰውየው በመጠጥ ቤቱ የፊት ለፊት በር በኩል ገብቶ ተቀመጠና መጠጥ አዘዘ።
መጠጥ ቀጂው ግን ሰውየው በጣም መስከሩን ስላዬ በትህትና ብዙ መጠጣቱንና ወደቤት ቢገባ እንደሚሻል ይነግረዋል።
ሰውዬው በስካር መንፈስ ቢሆንም በመጠጥ ቀጂው ንግግር ተገርሞ እሺ ብሎ እየተንገዳገደ በመጣበት በር ይወጣል።

ከትንሽ ቆይታ በኋላ በሌላ የጎን በር ድጋሚ እየተንገዳገደ ገባና መጠጥ አዘዘ።
መጠጥ ቀጂው አሁንም በትህትና ሌላ መጠጥ መጠጣት እንደማይችልና ከፈለገ ወደ ቤቱ ሊያደርሰው የሚችል መኪና ደውሎ ሊጠራለት እንደሚችል ይገልፅለታል።
ሰካራሙ ሰውዬ አሁን በንዴት መጠጥ ቀጂውን ካየው በኋላ እየተንገዳገደና እያጉተመተመ በመጣበት በር ይወጣል።

ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ በጓሮ በር በኩል ለሶስተኛ ጊዜ ወደ መጠጥ ቤቱ ይገባና መጠጥ ያዛል።
በዚህ ጊዜ መጠጥ ቀጂው በጣም ይናደዳል።
መጠጥ ቀጂው: "አንተ ሰውዬ ሰው የሚነግርህን አትሰማም እንዴ? ከመጠን በላይ ስለሰከርክ ተጨማሪ መጠጥ ልንሸጥልህ አንችልም አልኩህ እኮ።
አሁን ፖሊስ ጠርቼ ሳላስቀፈድድህ ከዚህ ቤት ውጣ። አላበዛኸውም እንዴ አሁንስ!!!" ሲለው
ሰካራሙ: መጠጥ ቀጂውን ቀና ብሎ ከተመለከተው በኋላ በብስጭት እያለቀሰ "አንተ ራስህ አላበዛኸውም እንዴ አሁንስ?
ቆይ ግን ስንት መጠጥ ቤት ነው የምትሰራው?" ብሎት እርፍ!!!

src:n/a

Comments

Popular Posts